Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ምርት ገበያው በ9 ወራት ከ30 ቢሊየን ብር በላይ የሚያወጡ ምርቶችን አገበያየ

አዲስ አበባ፣ሚያዝያ 22፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በ9 ወራት 602 ሺህ 823 ቶን ምርት ማገበያየቱ ተገለጸ።

በዚህም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በ30 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በማገበያየት የእቅዱን 97 በመቶ ማሳካቱ ተገልጿል።

ከዚያም ባለፈ የአዳዲስ መጋዘኖችና የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከላት ግንባታ ከ90 በመቶ በላይ መከናወኑ ነው የተገለጸው።

በተያያዘም የምርት ቅበላና ርክክብ ደህንነቱን ይበልጥ ለማረጋገጥም 36 የደህንነት ካሜራዎች በሦስት ቅርንጫፎች የተተከሉ ሲሆን፥ የገበያ መረጃን በተሻለ መንገድ ማሰራጨት የሚችሉ 66 የመረጃ ኪዎስኮች በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች እንዲቀመጡ ተደርጓል ነው የተባለው።

በዚህ የዘመናዊ የግብይት መድረክ 231 ሺህ 885 ቶን ቡና፣ 211 ሺህ 777 ቶን ሰሊጥ፣ 69 ሺህ 760 ቶን አኩሪ አተር፣ 46 ሺህ 914 ቶን አረንጓዴ ማሾ፣ 39 ሺህ 286 ቶን ነጭ ቦሎቄና 3 ሺህ 201 ቶን ቀይ ቦሎቄ ማገበያየቱ ነው የተነገረው።

ይህ ክንውን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃጸር በ100 ሺህ ቶን ወይም በ20 በመቶ ብልጫ እንዳለውም ተመላክቷል።

በምርት ስብጥር ሲታይ የቡና ግብይት የዕቅዱን 99 በመቶ ያሳካ ሲሆን፥ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንፃር ደግሞ ሁለት በመቶ ጨምሯልም ነው የተባለው።

በሌላም በኩል ሰሊጥ የዕቅዱን 75 በመቶ ያህል ሲገበያይ ከ2011 ተመሳሳይ ወቅት አንፃር የአራት በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

ከዚያም ባለፈ የምርት ገበያው 23ቱም ቅርንጫፎች ምርት የመረከብና ናሙና ወስዶ በላብራቶሪ በመፈተሽ ደረጃ የመስጠት ሥራቸውን አጠናክረው መቀጠላቸው ተገልጿል።

በዚህ መሰረት በዘጠኝ ወራት ውስጥ 64 ሺህ 033 ናሙና ተወስዶ ደረጃ መሰጠቱም ነው የተነገረው።

በሌላም በኩል የኮሮና ቫይረስ ስርጭት የውጭ ምንዛሬ ምንጭ በሆነው ዘመናዊ ግብይት ሥርዓቱ ሂደት ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድር ምርት ገበያ በዋናው መስሪያ ቤቱና በሁሉም ቅርንጫፎች ሠራተኞችንና ተገበያዮችን በማሳተፍ የመከላከል ሥራ እያከናወነ መሆኑ ተገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪም ኮሮና ቫይረስ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል እየተደረገ ያለውን አገራዊ ጥረት ለማገዝ የኢትዮጵያ ምርት ገበያና ሠራተኞቹ 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር መለገሱን ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!

https://t.me/fanatelevision

 

 

 

Exit mobile version