አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል ተከስቶ በነበረው ግጭት ምክንያት ለደረሱት የሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳቶች ምላሽ ሰጪ ዕቅድ ተግባራዊ በሚሆኑበት ሁኔታ ላይ ከአጋር አካላት ጋር የምክክር መድረክ ተካሄደ፡፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰላም ስምምነቱን መሰረት በማድረግ በትግራይ ክልል የደረሰውን ጉዳቱ በተመለከተ ስላለው ነባራዊ ሁኔታ መረጃዎችን የሚያሰባስብ ኮሚቴ በማዋቀር ወደ ስራ መገባቱ ተገልጿል።
የተገኘውን ተጨባጭ መረጃ መሰረት በማድረግ ምላሽ ሰጪ ዕቅድም እንደተዘጋጀ ነው የተጠቆመው፡፡
የምክክር መድረኩ እቅዱ ተግባራዊ በሚሆኑበት ሁኔታ ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ለመወያየትና ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ ነው ተብሏል፡፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አለሚቱ ኡሞድ÷እየተሰሩ ያሉትን ስራዎች ይበልጥ በማጠናከር በተቀናጀ መንገድ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ሚኒስቴሩ በቀጣይም በክልሉ የተቀናጀ ምላሽ ለመስጠት ለሚደረገው ጥረት ስኬታማነት አስፈላጊውን እገዛና ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
በምከክር መድረኩ ከተለያዩ የዓለም አቀፍ ተቋማት የተወከሉ የስራ ኃላፊዎች መሳተፋቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡