አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ በየትኛውም ዘርፍ ከምዕራባውን ጋር ለመፎካከር ዝግጁ ናት ሲሉ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ተናገሩ፡፡
ፕሬዚዳንት ፑቲን“ለመጪው ጊዜ አዲስ ሃሳብ” በተሰኘ ፎረም ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር÷የምዕራውያን ሀገራት በሩሲያ ላይ የጣሉት ማዕቀብ አዲስ የገበያ አማራጭ ይዞ መምጣቱን አንስተዋል፡፡
የሩሲያ ኩባንያዎች ከምዕራባውያን ጋር ለመወዳደር ዝግጁ ናቸው ያሉት ፕሬዚዳንቱ ÷ አብዛኞቹ ለፉክክሩ ብቁ መሆናቸው አሳይተዋል ብለዋል፡፡
ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን አጠናክሮ ለማስቀጠልም አዳዲስ ፖሊስዎች እና የገበያ አማራጮች እየተተገበሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አምስት ወራት 43 ሺህ ስራ ፈጣሪዎች የንግድ መለያ ምልክት ለመውሰድ መመዝገባቸውንም አንስተዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ፑቲን የሩሲያ ኩባንያዎች ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ለሀገር ውስጥ ብሎም ለዓለም አቀፉ ገበያ ተወዳዳሪ እና ጥራቱን የጠበቀ ምርት በማቅረብ እራሳቸውን ማሳደግ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡