አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ኢትዮጵያ ከ51 ሺህ በላይ የሱዳን ተፈናቃዮችን ተቀብላ እያስተናገደች መሆኑን ገልጿል።
ቋሚ ኮሚቴው በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውሀ እና መተማ ዮሀንስ አካባቢዎች በመጠለያ የሚገኙትን የሱዳን ተፈናቃዮች ጎብኝቷል።
ተፈናቃዮቹ የጸጥታ ስጋት እንዳይሰማቸው በሰሜን ምዕራብ ፈጥኖ ደራሽ የፌደራል ፖሊስ እና በኮማንድ ፖስት በጋራ አስተማማኝ ጥበቃ እየተደረገላቸው መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው መገንዘቡ ተገልጿል።
የቡድኑ አስተባባሪ ወይዘሮ ሥመኝሽ ሣህሉ÷ ከስደተኞች ቁጥር አኳያ የድጋፍ እጥረት እንዳይከሰት የረጂ ድርጅቶችን ቁጥር መጨመር አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ተፈናቃዮቹ በበኩላቸው÷የጸጥታ ስጋትም ሆነ የምግብ ችግር እንደሌለባቸው ገልፀው የውሀ እና የመጸዳጃ ቤት ችግር ግን እንዳለ መናገራቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡