አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ልማት ባንክ ከኢትዮጵያ እስከ ኬንያ በመሬት ውስጥ ለሚዘረጋ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መሥመር ዝርጋታ የ26 ሚሊየን ዩሮ ብድር አጸደቀ፡፡
በመሬት ውስጥ የሚዘረጋው 16 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የኃይል ማስተላለፊያ መሥመር 132 ኪሎ ቮልት የመሸከም ዐቅም ያለው ነው ተብሏል፡፡
ናንዩኪ እና ሩሙሩቲ የተሠኙትን ንዑስ የኃይል ማሠራጫ ጣቢያዎች ያገናኛል ነው የተባለው፡፡
የንዑስ ጣቢያዎቹ ግንባታም ቀጣዩ ዓመት ከመዘጋቱ በፊት ይጠናቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የአፍሪካ ልማት ባንክ በሁለቱ ሀገሮች መካከል የፕሮጀክት የኮንትራት ውል መፈጸሙን እና የቅድመ ንድፍ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡
ኬንያ ከባንኩ ተበድራ ግንባታውን ማከናወን የፈለገችው የሀገሪቷ የኃይል አቅርቦት ፍላጐት ዕድገት በማሳየቱ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
የመሥመር ዝርጋታውን ለማስጀመር ውሳኔ ላይ የደረሰችውም የዋጋ አዋጭነቱን በጥናት ለይታ መሆኑን በመረጃው ተጠቁሟል፡፡
የአሁኑ የኃይል ማስተላለፊያ መሥመር ግንባታ ፕሮጀክት የሚካሄደው 400 ኪሎ ቮልት የመሸከም ዐቅም ያለውን የማሪያካኒ ንዑስ ጣቢያ በፈረንጆቹ ጥር ወር ላይ አጠናቃ ሥራ ካስጀመረች በኋላ መሆኑንም የባንኩ መረጃ ያመለክታል፡፡
ኬንያ የሀገሪቷ የኃይል ፍጆታ እያደገ በመምጣቱ በጨረታ አወዳድራ ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል መግዛት የጀመረችው ባለፈው ዓመት መሆኑም ተመልክቷል፡፡
ሁለቱ ሀገራት ለ25 ዓመታት የሚዘልቅ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ተፈራርመዋል፡፡