አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 27 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ካዛኪስታን በሁለትዮሽ እና ባለ ብዙ ወገን መድረኮች ያላቸውን ትብብር ማጠናከር በሚችሉበት አግባብ ላይ ምክክር ተደረገ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከዛኪስታን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካናት ተሚሽ ጋር ፖለቲካዊ ምክክር አድርገዋል።
በዚህ ወቅትም በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ፣ በባለ ብዙ ወገን እና ሀገራቱ በትብብር ሊሰሩባቸው በሚችሉባቸው መስኮች ዙሪያ ምክክር ማድረጋቸውን በቱርክ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል።
አምባሳደር ምስጋኑ በዚህ ወቅት ምክክሩ የሀገራቱን የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ግንኙነት ብሎም ኢኮኖሚያዊ ትብብራቸውን ለማጠናከር ምቹ መደላድል እንደሚፈጥር እምነታቸውን መሆኑ ገልጸዋል።
አያይዘውም በሀገራቱ መካከል የተጀመረውን ፖለቲካዊ፣ ፀጥታ፣ ማህበራዊና ባህላዊ እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ አጋርነት ለማጠናከር እንደሚረዳም ጠቅሰዋል።
የካዛኪስታን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካናት ተሚሽ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ መንግስት ለቱርክ ላሳየው ድጋፍ እና የሀገራቱን ትብብር ለማጠናከር ላሳየው ቁርጠኝነት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።