Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በትግራይ ክልል የስምንተኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ከነገ ጀምሮ ይሰጣል-ትምህርት ቢሮ

 

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል የስምንተኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ከነገ ጀምሮ እንደሚሰጥ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የምዘናና የፈተናዎች ዳይሬክተር አቶ ክንፈ ፍስሃ እንደገለፁት÷ በክልሉ ከ60 ሺህ በላይ የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተናውን ይወስዳሉ።

ወላጆች ልጆቻቸውን ሙሉ ጊዜያቸውን ለትምህርት እንዲያውሉ ሲያግዙ መምህራን ደግሞ የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠትን ጨምሮ አሰፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ተማሪዎችን ለፈተናው አዘጋጅተዋቸዋል ብለዋል።

የተሰጣቸው የትምህርት ጊዜ አጭር ቢሆንም በ2012 ዓ.ም የመጀመሪያ መንፈቀ ትምህርት የተማሩ በመሆናቸውና በወላጅ መምህራን የተቀናጀ ጥረት ፈተናውን ለመውሰድ እንደማይቸገሩም አመልክተዋል።

በክልሉ በሚገኙ 78 ወረዳዎች የስምንተኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ከነገ ጀምሮ ለሶስት ለተከታተይ ቀናት እንደሚሰጥ ጠቅሰው ለዚህም በቂ ዝግጅት ተደርጓል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version