አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያቀረበውን ሪፖርት ማዳመጥ ጀምሯል፡፡
ትናንት የጀመረው የምክር ቤቱ 6ኛ የፓርላማ ዘመን፣ 2ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ፣ 2ኛ መደበኛ ጉባዔ ዛሬም ቀጥሏል፡፡
በዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቀድሞ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይኖሩ የነበሩ የስድስት ዞኖችና የአምስት ልዩ ወረዳዎች ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ያካሄዱትን ሕዝበ ውሳኔ አስመልክቶ ያቀረበውን ሪፖርት እያዳመጠ ነው፡፡
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ÷ ምክር ቤቱ ነሐሴ 12 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ውስጥ ይኖሩ የነበሩ የስድስት ዞኖችና የአምስት ልዩ ወረዳዎች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕዝበ ውሳኔ አስፈጽሞ ሪፖርት እንዲያደርግ መታዘዙን አስታውሰዋል፡፡
በዚሁ መሠረት ቦርዱ እያቀረበ ባለው ሪፖርት ላይ ውይይት እንደሚደረግ የፌዴሬሽን ምክር ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡