Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በዓለማችን እጅግ ሞቃታማው ቀን ትናንት ተመዘገበ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በዓለማችን እጅግ ሞቃታማው ቀን ትናንት መመዝገቡ ተገለጸ።

የአሜሪካ የአካባቢ ትንበያ ብሔራዊ ማዕከላት መረጃ እንዳመላከተው የዓለም አማካይ ሙቀት እንደትናንቱ ከፍ ብሎ አያውቅም፡፡

የትናንቱ አማካይ የዓለም ሙቀት 17 ነጥብ 01 ዲግሪ ሴሊሺየስ (62 ነጥብ 62ዲግሪ ፋራናይት) ሆኖ ነበር፡፡

ማዕከሉ ከዚህ ቀደም እጅግ ሞቃታማ ብሎ የመዘገበው አማካይ የዓለም ሙቀት 16 ነጥብ 92 ዲግሪ ሴሊሺየሽ (62 ነጥብ 46 ዲግሪ ፋራናይት) እንደነበረና በፈረንጆቹ 2016 ነኀሤ ወር ላይ እንደተመዘገበ አስታውሷል፡፡

ከቅርብ ሣምንታት ወዲህ የአሜሪካ ደቡባዊ ክፍል ነዋሪዎች በሙቀቱ ሳቢያ እየተሰቃዩ መሰንበታቸውም ተነግሯል፡፡

በቻይናም ሙቀቱ ከ35 ዲግሪ ሴሊሺየስ በላይ ሆኖ እንደቀጠለ ተነግሯል፡፡

የአፍሪካ ሰሜናዊ ክፍል እንዲሁ እስከ 50 ዲግሪ ሴሊሺየስ የሚደርስ ሙቀት አስመዝግቧል ነው የተባለው፡፡

በቀዝቃዛማነቱ የሚታወቀው የአንታርክቲካ ክፍል ሳይቀር ሙቀት ማስመዝገቡን ነው አልጀዚራ የዘገበው፡፡

ዓለም አቀፉ የዓየር ንብረት ለውጥ ተመራማሪ የሆኑት ፍሪዴሪክ ኦቶ አሁን እየሆነ ያለው የሚያስደስት ሳይሆን የሚያስደነግጥ ነገረ መሆኑን ገልጸዋል።

በዓየር ንብረት ላይ እየታየ ያለው ለውጥ እጅግ አስደንጋጭ እና በሰው ልጆች እና ሥነ ምህዳር ላይ የተወሰነ የሞት ፍርድ ውሳኔ ነው ብለዋል።

 

Exit mobile version