Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአማራ፣ አፋርና ትግራይ ክልሎችን ግንኙነት ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚያግዝ ውይይት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28 ቀን 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ፣ አፋርና ትግራይ ክልሎች መካከል ያለው ግንኙነት ቀድሞ ወደ ነበረበት ሁኔታ ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ ከክልሎቹ የሰላምና ፀጥታ እንዲሁም የትራንስፖርት ቢሮዎች አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

የሰላም የሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ካይዳኪ ገዛኸኝ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት በሰሜን የኢትዮጵያ ክፍል የነበረው ጦርነት ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተደረገው የሰላም ስምምነት ከተቋጨ በኋላ መንግሥት በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሰው እንዲቋቋሙ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል።

የሰላም ስምምነቱ እንዲፀና በየደረጃው ያሉ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ውይይት ማካሄድና እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማድረግ እንዳለባቸው አመልክተው የሶስቱ ክልሎች ህዝቦች በትራንስፖርትና በሌሎች ጉዳዮች እንዲቀራረቡ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

”የመንግስታት ግንኙነት አዋጅ” ፅንስ ሃሳብና አተገባበር ሰነድ በሰላም ሚኒስቴር የመንግስታት ግንኙነት ዴስክ ኃላፊ አቶ ግርማ ቸሩ በኩል ለመድረኩ ቀርቧል።

የሶስቱም ክልሎች የሰላምና ፀጥታ እንዲሁም የትራንስፖርት ቢሮ የሥራ ሀላፊዎች ውይይት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ እየተካሄደ እንደሚገኝ የሰላም ሚኒስቴር መረጃ ጠቁሟል።

Exit mobile version