አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገር አቀፍ የወሰንተሻጋሪ ወጣቶች በሐረሪ ክልል የተለያዩ የበጎ ፈቃድ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡
በጎ ፈቃድ ወጣቶቹ የችግኝ ተከላ፣ የማዕድ ማጋራት እንዲሁም የደም ልገሳ መርሐ ግብር ነው ያከናወኑት፡፡
የሐረሪ ክልሉ ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ደሊላ ዩሱፍ÷ የወጣቶቹ ተግባር የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ እንዲሁም ሰላም፣ ፍቅርን አንድነትን ለማጎልበት እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል።
መርሐ ግብሩ የባህልና የአኗኗር ልምድ የሚወሰድበት መሆኑን አንስተው÷ ይህም ወጣቱ ስለሀገሩ በጥልቅት እንዲረዳ እና ስብዕናውን በመልካም ሀሳቦች እንዲገነባ ያስችላል ብለዋል፡፡
በተለይም በወጣቶቹ በበጎ ፍቃደኝነት እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ደግነት ድንበር እንደሌለው የሚያመላክቱ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች እንደሚቀጥል መገለጹንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡