አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመተማመን ዘር፣ የመከባር ዘር እና የይቅርታን ዘር ያልዘራ ሰው የሰላም አዝመራን ማጨድ አይችልም ሲሉ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ዛሬ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ሰላምና ጸጥታን በተመለከተ በሰጡት ምላሽም፥ የጦርነት ሐሳብ የሚጎስሙ ሰዎች ሄደው የሚዋጉ እና በግንባር የሚገኙ አለመሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
እነዚህ አካላት የድሃ ልጆችን ጨምሮ ሌሎችን ለማስጨረስ ያለሙ መሆናቸውን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊገነዘብ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
ሰዎች ዝምብለው ሲቀሰቅሱ መከተል እንደሌለባቸውም ነው ያስረዱት፡፡
ሰላም አዎንታዊ አመለካከት ይፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ሰላም በሥራ እና በኢንቨስትመንት የሚገኝ መሆኑንም አውስተዋል።
“ጥርጣሬና ስድብ እየነዛን ሰላም ብንል አብሮ አይሄድም” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤት አባላት በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ።
ሰላም መከባበር እና መተጋገዝ እንዲሁም አንዱ ለአንዱ መተውን እንደሚፈልግ ጠቁመው÷ ይህን ሁሉም ሰው ሲያደርገው የተሟላ ሰላም ይገኛል ነው ያሉት፡፡
ጦርነት ትርፉ ጥፋት እንደሆነ በመጥቀስም በአንድ ቀን ብስጭት የሚጀመር እንዳልሆነም አንስተዋል፡፡
የትግራይ ሕዝብ የኢትዮጵያ አካል ስለሆነ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚያገኙትን ጥቅም ሊያገኝ እደሚገባም ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ከፕሪቶሪያው ስምምት በኋላ ቃል በተገባው መሠረት በሙሉ ልብ ሠርተናል፤ አሁንም እየሠራን ነው ብለዋል፡፡
በኤሌክትሪክ፣ በቴሌኮም እንዲሁም በእስረኞች መፈታት የተሠሩት ሥራዎች ለሠላም ሲባል መከናወናቸውን በማንሳትም፥ የሕወሓት ከአሸባሪነት ዝርዝር መነሳትም የዚሁ አካል መሆኑን አብራርተዋል።
በአማራ እና በአፋር ክልሎችም የተሠሩ ሥራዎች መኖራቸውን ገልጸው ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው በመመለስ ረገድ በርካታ ቀሪ ሥራዎች መኖራቸውን ነው የገለጹት።
በዮሐንስ ደርበው