Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ፕሮፐርቲ ታክስ በኢትዮጵያ አለመጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ

 

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2015 (ኤፍ ቢሲ) ሲ) ፕሮፐርቲ ታክስ ኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ መደረግ አለመጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አረጋገጡ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ፕሮፐርቲ ታክስን በተመለከተ የተነሳውን ጥያቄ በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ÷ አዲስ አበባ የራሱ ገቢ ያለው እና በራሱ የሚተዳደር ከተማ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ፕሮፐርቲ ታክስ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለመጀመሩ በአዲስ አበባም እንዳልተጀመረ ገልጸው፤ ከተማው የጀመረው ከዚህ ቀደም የነበረውን የጣሪያ እና ግርግዳ ግብር ህግ ዘንድሮም በማሻሻል እየተገበረ እንደሆነ ጠቁመዋል።

“ይህ የተሻሻለው የጣሪያ እና የግድግዳ ግብር ማለት ፕሮፐርቲ ታክስ ማለት አይደለም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ወደፊት የፕሮፐርቲ ታክስ አዋጅ በዝርዝር የሚታይ ጉዳይ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ከጣሪያና ግድግዳ ግብር ጋር በተያያዘ ያለው የታክስ ምንጭ በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ ጉዳት አምጥቶ ያልተገባ ሀብት ወስዶ ከሆነ ቅሬታ የሚሰማበት ስርአት ስላለ በዚያው ስርአት ቅሬታ ቀርቦ ሊታይ እንደሚችልም አስገንዝበዋል።

ፕሮፐርቲ ታክስ ካቢኔው አፅድቆ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ አዋጁ ፀድቆ ተግባራዊ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባ እየተሰበሰበ ያለው የጣራ እና የግድግዳ ግብር መሆኑንና ይህም ከ1937ዓ.ም ጀምሮ የመጣ እና ማሻሻያ የተደረገበት ነው ብለዋል፡፡

በፌቨን ቢሻው

Exit mobile version