Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ፍርድ ቤቱ በቀድሞ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በእነ ቴድሮስ በቀለ ላይ የቀረቡ ምስክሮችን አዳምጦ አጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በከባድ ሙስና ወንጀል በተከሰሱት በቀድሞ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ በቀለ ላይ የቀረቡ ምስክሮችን አዳምጦ አጠናቀቀ።

ፍርድ ቤቱ ቴድሮስ በቀለን ጨምሮ በሰባት ግለሰቦች ላይ ተመስርቶ በነበረው የከባድ ሙስና ወንጀል ክስ መነሻ ነው የዐቃቤ ህግ ምስክሮችን ቃል አዳምጦ ያጠናቀቀው።

ዐቃቤ ህግ በተከሳሾቹ ላይ ካቀረባቸው አጠቃላይ ስምንት ምስክሮች መካከል የመረጣቸውን ስድስት ምስክሮችን የምስክርነት ጭብጥ በማስመዝገብ የምስክርነት ቃላቸውን አሰምቷል፤ከተሰሙ ምስክሮች መካከል የሙያ ምስክሮች ይገኙበታል።

ዐቃቤ ህግ በጥር 2 ቀን 2015 ዓ.ም ባቀረበው የከባድ የሙስና ወንጀል የክስ ዝርዝር ላይ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ቴድሮስ በቀለ፣ ተከሳሽ የአቶ ቴድሮስ ባለቤት ሩት አድማሱ፣ የወ/ሮ ሩት እህት ቤተልሔም አድማሱ እና በግል ሥራ ይተዳደራሉ የተባሉት መርሃዊ ምክረ ወልደፃዲቅ ፣ራሄል ብርሃኑ፣ ፀሐይ ደሜ እና ጌታቸው ደምሴ የተባሉ ግለሰቦች የወንጀል ተሳትፎ ተጠቅሶ ነበር ያቀረበው።

በዚህም ቀርቦ በነበረ ክስ በ1ኛው ክስ ላይ እንደተመላከተው አቶ ቴድሮስ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሲሠሩ የተቋሙን አሠራር ባልተከተለ መልኩ አስፈላጊው የደኅንነት ይለፍ ያልተደረገለትን የትምህርት ዝግጅቱ ብቁ ያልሆነና በሌላ የሙስና ወንጀል መዝገብ የተከሰሰ አቤል ጌታቸው የተባለ ግለሰብን ከታኅሣሥ 1ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በተቋሙ የተደራጁና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ወንጀሎች ፍተሻና ትንተና ከፍተኛ ኤክስፐርት ሆኖ እንዲሠራ ወደ ተቋሙ እንዲቀላቀል አድርገዋል በማለት ዘርዝሮ ነበር።

እንዲሁም ከሰኔ 1ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ አቤል ጌታቸው የተባለን ግለሰብ የፋይናንስ መረጃ ክትትል እና ቅበላ ቡድን መሪ አድርገው ባልተገባ መንገድ መድበዋል በማለት በክሱ አመላክቷል፡፡

በተጨማሪም የተቋሙን የቀደመ የመረጃ ሚስጢራዊነት የጠበቀ እና ተጠያቂነትን ያማከለ የመረጃ ቅበላ እና ትንተና አሠራርን በመለወጥ፣ በተቋሙ ውስጥ ስልጣንን ተገን በማድረግ፣ የባለሃብቶችንና የድርጅቶችን የባንክ ሂሳብ አስቀድሞ በማጥናትና መረጃ በመውሰድ፣ በተለያየ ጊዜ ለባለሀብቶች ስልክ በመደወል በአካል በማግኘት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እንዲከፍሉ በመጠየቅ፣ የማይከፍሉ ከሆነ ደግሞ የፋይናንስ እንቅስቃሴያቸውን በተመለከተ ምርመራ አድርጎ ለፖሊስ በማስተላለፍ የወንጀል ምርመራ እንዲጀመርባቸው እንዲደረግ ይገልፅ እንደነበረ በክሱ ጠቅሷል።

ተከሳሹ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ውስጥ የነበረውን ኃላፊነት በመጠቀም፣ የፋይናንስ ትንተና በመሥራት ውጤቱን ለፍትሕ አካላት የሚተላለፍ ስልጣንን አላግባብ በመጠቀም፣ ገንዘብ ያላቸው ባለሃብቶችን አስቀድሞ በማጥናት በመምረጥ በ2013 እና በ2014 ዓ.ም በተለያየ ጊዜ ባለሃብቶች የባንክ ሒሳባቸው እንደሚታገድ እና በፖሊስ እንደሚመረመሩ በመግለጽ በማስፈራራት ከሦስት ግለሰቦች 3 ሚሊየን 470 ሺህ ብር በፋፋ ዳባ በተባለ ስም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገቢ እንዲደረግ በማድረግ በዋና ወንጀል አድራጊነት ስልጣንን አለአግባብ መገልገል ከባድ ሙስና ወንጀል ተከሰዋል።

ሁለተኛ ክስ ደግሞ በሁሉም ተከሳሾች የቀረበ ሲሆን÷በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ሀ እና በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ሕጋዊ አድርጎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን በሚል ክስ መቅረቡ ይታወሳል።

ተከሳሾቹ ይህን የቀረበባቸውን የከባድ ሙስና ወንጀል ክስ አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው በሰጡት የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ነው ከሳሽ ዐቃቤ ህግ ስድስት ምስክሮችን አቅርቦ ያሰማው።

ፍርድ ቤቱ የምስክሮች ቃል ሰምቶ ዛሬ ከሰዓት በኃላ አጠናቅቋል።

የተሰማው የምስክሮች ቃል ወደ ፅሁፍ ተገልብጦ ከመዝገቡ ጋር እንዲያያዝ በማዘዝ የሰነድ ማስረጃዎች በሚመለከት አስተያየት ለመቀበል ፍርድ ቤቱ ለሐምሌ 20 ቀን 2015 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version