አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 30 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝባችንን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ፥ “እንደ ክልላችን ላለፉት ዓመታት የተገነቡት ልማታዊ ፕሮጀክቶች በጥራት እና በፍጥነት ከመሰራታቸው በተጨማሪ ከተያዘላቸው ጊዜ ቀድሞ መጨረስን ባህል ያደረጉ ናቸው” ብለዋል፡፡
በለውጡ መጀመሪያ ላይ “የማናጠናቅቀውን ስራ አንጀምርም” በሚል መርህ “እንደገባነው የጀመርናቸውን ፕሮጀክቶች በማጠናቀቅ ሪቫን መቁረጥ ባህል አድርገናልም” ነው ያሉት፡፡
ላለፉት ዓመታት በሺህዎች የሚቆጠሩ ፕሮጀክቶችን ሰርተን ለህዝብ ጥቅም እንዳዋልነው ሁሉ በዚህ ዓመትም እየተሰሩ ካሉት 29 ሺህ 762 ፕሮጀክቶች ውስጥ 19 ሺህ 912 ፕሮጀክቶችን አጠናቅቀን አስመርቀናል ብለዋል።
ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ናቸው ያሉት አቶ ሽመልስ፥ ይህም መንግስት ለህብረተሰቡ ተጠቃሚነት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን እንደሚያሳይ አንስተዋል።
በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች ውስጥ ያሉ የለውጥ አመራሮችም እየጨመረ የመጣውን የልማትና የለውጥ ፍላጎት ምላሽ ለመስጠትና የተያዘውን የብልጽግና እቅድ ለማሳካት ላለባቸው ድርብ ኃላፊነት እንዲዘጋጁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡