አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ግብር የመሰብሰብ አቅምን ማሳደግ ለሀገር ልማትና እድገት ወሳኝ ነው ሲሉ የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ ገለጹ፡፡
የገቢዎች ሚኒስቴር የመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቁጥር ሁለት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር አካሂዷል፡፡
“በሜክሲኮ” አካባቢ የሚገኘውና ዛሬ በይፋ ሥራ የጀመረው የመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽ/ ቤት ለ4 ሺህ 77 ግብር ከፋዮች አገልግሎት እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡
የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ÷ የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ መከፈት ግብር ከፋዩ በአቅራቢያው የተሳለጠ አገልግሎት እንዲያገኝ ያስችለዋል ብለዋል።
ቅርንጫፉ ተመሳሳይ እና ተቀራራቢ የህግ ተገዢነት ደረጃና ባህሪ ላላቸው ግብር ከፋዮች አንድ ላይ አገልግሎት እንዲሰጥ በማድረግ ውጤታማና ወጪ ቆጣቢ የገቢ አሰባሰብን ተግባራዊ እናደርጋለን ሲሉም ተናግረዋል።
የተቀላጠፈ አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር ገቢን አሟጦ መሰብሰብ እንዲቻል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ እንዲደራጅ አስፈልጓል ነው ያሉት።
እንደ ሀገር የግብር መሰብሰብ አቅምን ማሳደግ ለሀገር ልማትና እድገት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው÷ ለግብር ከፋዮች ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ያስፈልጋል ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡