Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በደቡብ ክልል በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ2 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ወጣቶች እንደሚሳተፉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል ከ2 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ወጣቶች በዘንድሮው የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ ላይ እንደሚሳተፉ የክልሉ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የደቡብ ክልል የወጣት አደረጃጀቶች የ2015 የክረምት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በቡታጅራ ከተማ እየተካሔደ ነው ፡፡

የክልሉ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ም/ ሃላፊ ሙስጠፋ ኢሳ እንደገለጹት÷ወጣቶች እምቅ አቅም፣ ክህሎትና እውቀት፣ እንዲሁም አዳዲስ ሀሳቦች ችሎታ ያላቸው በመሆኑ በሁሉም የልማት መስኮች ስኬታማ ተግባር እያከናወኑ ነው፡፡

ወጣቶች በክልሉ በየዓመቱ በሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ያልተሸፈኑ የህብረተሰብ እና የመንግስት የልማት ፍላጎቶችን ለማሟላት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በችግኝ ተከላ፣ አቅመ ዳካማ የህብረተሰብ ክፍሎችን መደገፍ፣ በደም ልገሳ እና በሌሎች የስራ ዘርፎች እንደሚሳተፉ አብራርተዋል።

በክልሉ በ2015 ዓ.ም የክረምት የጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ ግብር ከ2 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ወጣቶች እንደሚሳተፉም የቢሮው መረጃ ያመላክታል፡፡

በ11 የስራ ዘርፎች የሚከናወነው የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት÷ ከ2 ቢሊየን በላይ የሚገመት ብር ማዳን እንደሚያስችልም ተነግሯል።

በበጎ ፈቃድ ማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ፣የደም ልገሳ እና የጽዳት ዘመቻ ስራዎች ተከናውነዋል።

Exit mobile version