አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 3 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ተፈጽሟል በተባለ የግብዓት ግዢ ከ40 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት ማድረስ የሙስና ወንጀል በተጠረጠሩ ስድስት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ስራ አመራር ኮሚሽን ሰራተኞች ላይ ክስ የመመስረቻ ጊዜ ተፈቀደ።
ክስ መመስረቻ ጊዜ የፈቀደው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው።
ተጠርጣሪዎቹ በአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከል ስራ አመራር ኮሚሽን የግዢ ኮሚቴዎች ናቸው የተባሉት ግሩም ወልዴ፣ ደረጄ ተፈራ፣ ወንድሜነህ ምስጋናው፣ ዘውዱ ተፈራ ደገፋ፣ እዮብ ታደሰ ካሳ እና አልማዝ ጌቶ ናቸው።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ በተጠርጣሪዎች ላይ በ2011 ዓ.ም በተፈረመ በግዢ ጨረታ ሰነድ መነሻ በ2014 ዓ.ም በጀት አመት ለተቋሙ የአደጋ መቆጣጠሪያ ግብዓቶችን የግዢ የጨረታ ስርዓቱን ባልተከተለና የገበያ ጥናት ባልተደረገበት ሁኔታ ላይ በተፈጸመ ግዢ ከ40 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት ደርሷል በማለት ፖሊስ ምርመራ ሲያከናውን መቆየቱን አስታውቆ ነበር።
በዛሬው ቀጠሮ ደግሞ የፌደራል ፖሊስ መርማሪ የምርመራ ስራውን ማጠናቀቁን እና የምርመራ መዝገቡን ለዐቃቤ ህግ ማስረከቡን ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ይፋ አድርጓል።
የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ በበኩሉ የምርመራ መዝገቡን ተመልክቶ በወ/መ/ስ/ህ/ቁጥር 109 መሰረት ክስ መመስረት እንዲያስችለው የ15 ቀን ክስ የመመስረቻ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል።
ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው በ2011 ዓ.ም የግዢ ኮሚቴ አባል እንዳልነበሩ ጠቅሰው ተፈጽሟል ለተባለው ጉዳት አስተዋጽኦ የለንም በማለት ተከራክረዋል።
” የተሻለ አፈጻጸምና ሥነምግባር አላችሁ ተብለን ወደ ግዢ ኮሚቴ አባል ተደርገናል ” በማለትም ተጠርጣሪዎቹ ምንም ወንጀል አለመፈጸማቸውን ገልጸው ተከራክረዋል።
የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን የጠቀሱት ተጠርጣሪዎቹ የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ጠይቀዋል።
በኃላፊ ከ2014 በጀት አመት አስር ከመቶ ተቀናሽ እንዲደረግ በተሰጠ ትዕዛዝ መሰረት እንዲፈጸም አድርገናል በማለት አስተያየት የሰጠች ተጠርጣሪ ነበረች።
የተጠርጣሪዎችን መከራከሪያ ነጥብ ተከትሎ ዐቃቤ ህግ የተገኙ ሰነዶችና የኦዲት ሪፖርት የሚያሳየው በ2011 ዓ.ም የተፈረመ የጨረታ ሰነድ ላይ የግዢ ኮሚቴ አባሎች የነበሩ ተጠርጣሪዎች ውሳኔና ፊርማ ያለአግባብ ግዢ መፈፀሙንና በዚህም ከ40 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት በመንግስት ላይ ደርሷል በማለት መልስ ሰጥቷል።
በተጨማሪም ዐቃቤ ህግ ከደረሰው ጉዳትና ማስረጃዎች አንጻር ዋስትና በሚያስከለክል በከባድ የሙስና አንቀጽ ክስ እንደሚመሰርት ጠቅሶ የዋስትና ጥያቄያቸውን በመቃወም ተከራክሯል።
አቆያየታቸውን በሚመለከት ክስ እስከሚመሰረት በማረፊያ ቤት እንዲቆዩ ዐቃቤ ህግ ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱን ጠይቋል።
የግራ ቀኝ ክርክሩን የመረመረው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ተጠርጣሪዎቹ ላይ ክስ የመመስረቻ ጊዜ መስጠት አስፈላጊነትን በማመን የተጠርጣሪዎቹን የዋስትና ጥያቄ በማለፍ ዐቃቤ ህግ ከጠየቀው 15 ቀን ክስ የመመስረቻ ጊዜ ውስጥ የ10 ቀን ጊዜ ፈቅዷል።
በታሪክ አዱኛ