አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ወጣቶች በትግራይ ክልል እንደርታ ወረዳ በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰበት ደብረ መድኃኒት ት/ቤት የግንባታ ግብዓት ድጋፍ አደረጉ፡፡
ከግንባታ ግብዓት ድጋፉ በተጨማሪም አረንጓዴ ዐሻራ የማኖር እና ለሕጻናት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተከናውኗል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የወጣቶች ቢሮ ኃላፊ ሀይሽ ስባጋዲስ÷ ወጣቶቹ ክልሉን መጎብኘታቸው ለበጎ ፈቃድ አገልገሎት መነቃቃት ይፈጥራል ብለዋል፡፡
በቀጣይም ትምህርት ቤቱን በአዲስ መልክ ለመገንባት÷ ወጣቶቹ በሚሄዱበት አካባቢ ሁሉ የአቅማቸውን ድጋፍ እንዲያሰባስቡ ጠይቀዋል።
የእንደርታ ወረዳ አስተዳዳሪ ብርሃነ ዮሐንስ በበኩላቸው÷ በወረዳው የወሰን ተሻጋሪ ወጣቶች የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ ተግባር ለተፈጥሮ ሐብት ጥበቃና እንክብካቤ ሥራ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።
የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩም ከዛሬ ጀምሮ በንቅናቄ ደረጃ ክረምቱን ሙሉ ይከናወናል ነው ያሉት፡፡
በጎህ ንጉሱ