Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የብሔራዊ መታወቂያ ትግበራ የተጠናከረ የፋይናንስ ዘርፍ ለመገንባት እንደሚያስችል ተመለከተ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሔራዊ መታወቂያ ትግበራ የገንዘብ መጭበርበርን በመቀነስ፣ የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነትን በመጨመር እና የተሻሻለ የደንበኞችን የማንነት ማረጋገጫ ሥርዓት በመዘርጋት የተጠናከረ የፋይናንስ ዘርፍ ለመገንባት ያስችላል ተባለ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በመተባበር “ዲጂታል መታወቂያ ለፋይናንስ ዘርፍ” የሚል ፕሮጀክት ትግበራ መጀመሩን አስታውቋል፡፡

በዲጂታል መታወቂያ ትግበራ ዙሪያም ሁለት መርሐ ግብሮችን መጀመሩን የገለጸው ባንኩ፤ የመጀመሪያው መርሐ ግብር÷ ሁሉም የፋይናንስ ተቋማት ደንበኞቻቸውን በ2016 በጀት ዓመት ወደ ዲጂታል መታወቂያ ስርዓት በማስገባት የተሻለ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ መሆኑን አመልክቷል።

ዓላማውም÷ ለሀገሪቱ ነዋሪዎች የፋይናንስ አገልግሎቶችን ተደራሽነት ማስፋፋት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ሂደቱም የተመዝጋቢውን ግላዊ መረጃዎች ጥበቃ ቅድሚያ በመስጠት እና የመረጃ ደኅንነትን በማረጋገጥ እንደሚከናወን ነው የተመለከተው፡፡

ይህ ሲሆን እስከ ዛሬ ድረስ የተሰጡትም ሆነ ከዚህ በኋላ በዚህ ሥርዓት የሚሰጡ የዲጂታል መታወቂያዎች በሀገሪቱ በየትኛውም የፋይናንስ ተቋማትም ሆነ ዲጂታል ሥርዓቶች ተቀባይነት አላቸው ነው የተባለው፡፡

ሁለተኛው መርሐ ግብር÷ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሳለጥ እና የፋይናንስ ሥርዓት ደኅንነትን ለማስጠበቅ በማቀድ በዘርፉ በኤሌክትሮኒክ ደንበኛህን እወቅ (ekYC) ሂደት ውስጥ የዲጂታል መታወቂያን መጠቀም ነው።

ይህ አካሄድ የፋይናንስ አገልግሎቶች ተጠቃሚን ትክክለኛ ማንነት በማረጋገጥ የፋይናንስ ግብይቶች ደኅንነትን ለመጠበቅ እና ተያያዥ ስጋቶችን በእጅጉ ለመቀነስ እንደሚያስችል ተጠቅሷል፡፡

በተጨማሪም አንድን የሀገሪቱ ነዋሪ በአካል መምጣት ሳያስፈልግ በዲጂታል አማራጭ ብቻ ደንበኛ ለማድረግ ያስችላል መባሉን የባንኩ መረጃ ያመላክታል፡፡

የዲጂታል መታወቂያ በፋይናንስ ዘርፍ መተግበር÷ በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ ግልጽነትን እና አካታችነትን በማጎልበት ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ነው የተመለከተው፡፡

የጋራ መርሐ ግብሩ ኢትዮጵያ ወደ ላቀ የዲጂታል ፋይናንስ ሥነ ምህዳር ለምታደርገው ጉዞ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ታምኖበታል፡፡

Exit mobile version