አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ አፍሪካ ቅዝቃዜው በማየሉ ሥራ ለመሥራት እንኳን እጅግ እንደተቸገሩ ነዋሪዎቹ እየተናገሩ ነው፡፡
በተለይም የሰሜናዊ ኬፕ መዲና የሆነችው የኪምበርሊ ከተማ አንዳንድ ነዋሪዎች በቅዝቃዜው ሳቢያ መሥራት እንዳልቻሉ ገለጸዋል፡፡
በሀገሪቷ የሚኖሩ የጎዳና ተዳዳሪዎችም መጠለያ ፣ ብርድ ልብስም ሆነ የክረምት ልብስ ስለሌላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እንዲሁም የሀገሪቷ የማኅበራዊ ጉዳዮች እና ልማት መምሪያ እርዳታ እንዲያደርጉላቸው መጠየቃቸውን ኤስ ኤ ቢ ሲ ዘግቧል፡፡
ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ከኪምበርሊ በተጨማሪ በሱዌቶ ከተሞች የሚኖሩ ነዋሪዎችም ምንም እንኳን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ቢቋረጥብንም ራሳችንን ቤተለያዩ ዘዴዎች ለማሞቅ እየታገልን ነው ብለዋል፡፡
በሱዌቶ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የተቋረጠበት ምክንያት እስካሁን አለመታወቁንም ዘገባው አመላክቷል።
የደቡብ አፍሪካ የአየር ሁኔታ ትንበያ አገልግሎት በሀገሪቱ አንዳንድ ክፍሎች ቅዝቃዜ እንደሚኖር ቀደም ብሎ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል ነው የተባለው።
አሁን የተከሰተው ከፍተኛ ቅዝቃዜ ምናልባት ለቀናት ሊቀጥል እንደሚችልም ነው የተነገረው።