አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁሉንም የልማት አቅምን በማቀናጀትና የግል ኢንቨስትመንት ዘርፉን በማበረታታት ኢኮኖሚውን ማሻሻል ይገባል ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል (ዶ/ር) ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ የሚገኘውን ገደፋው ይስማው አውቶሞቲቭና ትሬለር ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ መጎብኘታቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
ኢንዱስትሪው ከባድ ተሽከርካሪዎችን በመገጣጠምና ሌሎች የኢንዱስትሪ ግብአቶችን አምርቶ ለተጠቃሚዎች በማቅረብ ለዘርፉ ዕድገትና ለኢኮኖሚው መሻሻል ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል፡፡
ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠሩንም ነው ያመላከቱት፡፡
በተጨማሪም የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማዕከል በመሆኑ በቀጣይ በቴክኖሎጂ አቅሙ፣ በጥራትና በምርታማነት ደረጃው ተወዳዳሪ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡