አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 480 ሚሊየን ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያላቸው ችግኞች እንደሚተከሉ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ሃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ እንደገለጹት÷ በክልሉ የፊታችን ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም በአንድ ጀምበር 480 ሚሊየን ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያላቸው ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል።
በመርሐ ግብሩም ለምግብነት የሚውሉትን ጨምሮ የደን ሽፋን ለማሳደግ የሚውሉ ችግኞች ወደ መትከያ ቦታ የማጓጓዝ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው÷ የጉድጓድ ዝግጅት እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።
በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አርብቶ አደሩና አርሶአደሩን ጨምሮ መላው የክልሉ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የጨፌ ኦሮሚያ አባላት በበኩላቸው÷ የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብርን ለማሳካት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
ሐምሌ 10 በሚካሄደው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እንዲሳካ የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አባላቱ ገልጸዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ ከልጆች ጀምሮ ሁሉም በየደረጃው ያለው የህብረተሰብ ክፍል እንዲሳተፍ ህዝቡን የማንቃት ስራ እየሰሩ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡