አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በዘንድሮው የክረምት ወራት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር 2 ሚሊየን ችግኝ እንደሚተከል የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ፡፡
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ብሩክ ፈለቀ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ ሰኔ 25 ቀን የተጀመረው ምዕራፍ ሁለት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እስከ ነሐሴ መጨረሻ 2015 ዓ.ም ድረስ ይቀጥላል፡፡
ለዚህም በአብዛኛው ለጥላ እና ደን የሚሆኑ እንዲሁም የፍራፍሬ ችግኞች መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል፡፡
በአጠቃላይ በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩም በከተማ እና በገጠር ከ160 ሺህ በላይ የአስተዳደሩ ነዋሪ እንደሚሳተፍ ጠቁመዋል፡፡
የፊታችን ሰኞም በአንድ ጀምበር 800 ሺህ ችግኝ እንደሚተከል ነው የገለጹት፡፡
በዮሐንስ ደርበው