አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ‘‘በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ’’ በሚል መሪ ሀሳብ የደቡብ ክልል የዘንድሮው የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሔደ፡፡
በክረምት ወራት በሚከናወነው የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ ላይ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳ፣ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ፋጤ ስርሞሎ እና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ርዕሰ መስተዳደር ርስቱ ይርዳ በወቅቱ÷የበጎ አድራጎት ስራ ብዙ አቅመ ደካሞች የተደገፉበትና በመንግስት አቅም የማይቻል ወጭ የተሸፈነበት በመሆኑ ተሳታፊ ወጣቶችን አመስግነዋል፡፡
በክልሉ ባለፉት ጊዜያት ከ10 ሺህ በላይ የአቅመ ደካሞች ቤት ማደስ ስራ በክረምት ወራት በጎ አድራጎት አገልግሎት መሰራቱን ገልፀዋል።
ባለፈው አመት የክረምት የወጣቶች በጎ አድራጎት ሥራ 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ከመንግስት የሚወጣ ገንዘብን ማስቀረት መቻሉንም ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቅሰዋል፡፡
የክረምት የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎትመርሐ ግብሩ ከ2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ወጪማዳን ያስችላል ተብሏል።
በማሕሌት ኡኩሞ