አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 43ኛው የአፍሪካ ህብረት ስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ በኬንያ ናይሮቢ እየተካሄደ ይገኛል።
በጉባዔው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ የተመራ ከፍተኛ የልኡካን ቡድን እየተሳተፈ ነው።
የኬንያ የውጭ ጉዳይና የዲያስፖራ ጉዳዮች ሚኒስትር አልፍሬድ ሙቱዋ(ዶ/ር) የስራ አስፈፃሚ ስብሰባውን በንግግራቸው ሲከፍቱ እንዳሉት ፥ አፍሪካ በተፈጥሮ ሀብቶች የበለፀገች ብትሆንም በልማት ብዙ የሚቀሩ ጉዳዮች እንዳሉ ጠቅሰዋል ።
በመሆኑም የአፍሪካ ሀገራት ውህደታቸውን ለማፋጠን በሰዎችና በሸቀጦች ላይ ያላቸውን የእንቅስቃሴ ገደብ እንዲያነሱ የጠየቁ ሲሆን ፥ ኬንያ ለአፍሪካውያን የቪዛ ጉዳይን በሂደት ለማስወገድ ዝግጁ መሆኗን አስታውቀዋል።
የኮሞሮስ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር እና የወቅቱ የስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ሊቀመንበር ዶሂር ዱልቃማል በበኩላቸው ፥ የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መደረጉ ለአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ውህደት ጠቃሚ ነው ብለዋል።
ስብስባው የሚደረገው “የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራን ማፋጠን” በሚል መሪ ሃሳብ መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ።