አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግሥት የሴቶችን የመሪነት አቅም ለማሳደግ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።
የፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ከዩ ኤን ውመን ጋር በመተባበር ለሴት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በአቅም ግንባታና የሴቶችን አመራር ጥበብ ማሳደግ ላይ ያተኮረ ሥልጠና እየሰጠ ነው።
ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በሥልጠናው መክፈቻ ላይ እንዳሉት÷ ሴቶች ለሰላምና ልማት ትልቅ አቅም ቢሆኑም ባላቸው በተፈጥሮ የመረዳት፣ የማገናዘብ፣ ትዕግሥትና አዛኝነት ልክ የመወሰን ዕድል ሳይሰጣቸው ቆይቷል።
ሴቶች የቤተሰብ ምሰሶ ሆነው ችግርን ቀድመው የመረዳ ብቃት ያላቸው በመሆኑ ሴት የምክር ቤት አባላት ለሀገርና ለሕዝብ ቅድሚያ በመስጠት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በራስ መተማመን ለሴቶች እንደ ድፍረት የሚቆጠርበት ብሂል መወገድ አለበት ያሉት ፕሬዚዳንቷ÷ ሴቶች ኃላፊነታቸውን በመወጣት ተጽዕኖ መፍጠር እንዳለባቸው ገልፀዋል።
መንግሥት በተለያዩ ተቋማት የሴቶችን የመሪነት ሚና እያሳደገ እንደመጣ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡