አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሰመረታ ሰውሰው ከአየርላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና ፀሃፊ ጆሴፍ ሃኬት ጋር የሁለቱ ሀገራትን ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
በውይይታቸው ሚኒስትር ዴኤታዋ ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ በኢትዮጵያ በሰላም እና በኢኮኖሚ ዘርፎች እየመጡ ያሉ ለውጦቸን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
መንግስት ፈጣን እና ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥ እንዲሁም ተፈጥሯዊ አደጋዎችን ለመቀነስ እየወሰዳቸው የሚገኙ እርምጃዎችን በተመለከተም ገለጻ አድርገዋል፡፡
ዋና ፀሃፊ ጆሴፍ ሃኬት በበኩላቸው አየርላንድ በግብርና ልማት እና በሰላም ግንባታ ዘርፎች ላይ ያላትን ተሞክሮ አካፍለዋል።
አየርላንድ ባለፉት አምስት አመታት በጤና፣ ግብርና እና ማህበራዊ ጥበቃ ዘርፎች ለኢትዮጵያ በርካታ ድጋፎችን ስታደርግ መቆየቷን አስታውሰዋል፡፡
በውይይቱ የሁለቱ ሀገራትን ግንኙነት በአዲስ መልክ ለማሳደግ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡