Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አቶ ደመቀ መኮንን ከደቡብ አፍሪካ እና ከቻድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር መከሩ

 

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከደቡብ አፍሪካ የአለም አቀፍ ግንኙነት እና ትብብር ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር እና ከቻድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማህማት ሳሌህ አናዲፍ ጋር በኬንያ ናይሮቢ ተወያይተዋል ።

አቶ ደመቀ ለሚኒስትሮቹ ስለ ፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ተስፋ ሰጪ አፈፃፀም እና ኢትዮጵያ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽኖችን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እየሰራች ስለመሆኑ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በውይይቱ የደቡብ አፍሪካ የአለም አቀፍ ግንኙነት እና ትብብር ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር÷ ደቡብ አፍሪካ የሰላም ማስፈጸሚያ እቅዶች ተግባራዊ እንዲሆኑ ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗን ተናግረዋል ።

በተመሳሳይ አቶ ደመቀ መኮንን ከቻድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማህማት ሳሌህ አናዲፍ ጋር ተገናኝተው በሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

ሁለቱ ሚኒስትሮች ግንኙነታቸውን ለማጠናከር መስማማታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

43ኛው የአፍሪካ ኀብር የስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ በኬንያ ናይሮቢ እየካሄደ ይገኛል ።

 

 

 

Exit mobile version