Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከ410 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ የወጣቶችና የህፃናት የስፖርት ማዘውተሪያዎችን መረቁ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 8 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ 24 ዘመናዊ የወጣቶችና የህፃናት የስፖርት ማዘወተሪያዎችን አስመርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።

 

የስፖርት ማዘውተሪያዎቹ በ410 ሚሊየን 217 ሺህ 800 ብር የተገነቡ መሆኑን ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል።

 

ማዘውተሪያዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አዲስ አበባን ለዛሬና ለነገው ትውልድ ምቹ ለማድረግ፣ ልጆች እንደልባቸው የሚቦርቁባት፣ በየአካባቢያቸው በቂ የመጫወቻ እና ስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ እንዲኖራቸው ለማድረግ ባበረከቱት “የመደመር ትውልድ” መፅሐፍ የሰጡትን አደራ በመቀበል መገንባታቸውንም አስታውቀዋል።

 

ሰባቱ የወጣት የስፖርት ማዘውተሪያ እና የህፃናት መጫወቻ በ110 ሚሊየን ብር “ከመደመር ትውልድ” መፅሐፍ ሽያጭ በተገኘ ገንዘብ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ የተገነቡ ሲሆን፥ ቀሪዎቹ 17 ፕሮጀክቶች ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ከ300 ሚሊየን በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባቸው መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

 

ይህም ልጆች በአካል እና በአዕምሮ የበለጸጉ ሆነው እንዲያድጉ ለማድረግ የተሰጠውን ትኩረት ያሳያል ነው ያሉት።

 

ከንቲባዋ አያይዘውም “በዚህ በጀት ዓመት ብቻ በአዲስ አበባ እስካሁን ድረስ ከ5 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ለመረጠን ህዝብ በትጋትና በታማኝነት ማገልገላችንን አረጋግጠናል” ብለዋል።

Exit mobile version