Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሙሽራ ሸኝተው ሲመለሱ በነበሩ ሰዎች ላይ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የሟቾች ቁጥር 10 ደረሰ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በስልጤ ዞን ምዕራብ አዘርነት በርበሬ ወረዳ ጃረሞ ሰምቦዬ ቀበሌ ጀኔ ማዞሪያ አካባቢ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የሟቾች ቁጥር አሥር መድረሱን የዞኑ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ሟቾቹ የሥጋ ዝምድና እንዳላቸው እና ከነዚህ ውስጥ እናትና ልጅ እንደሚገኙበትም ነው የተገለጸው፡፡

የስልጤ ዞን ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኮማንደር ሸምሱ ኢክማ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት÷ አደጋው የደረሰው ትናንት ምሽት በግምት 5፡00 ገደማ ነው፡፡

አደጋው የደረሰባቸው ሰዎችም ሙሽራ ሸኝተው ወደ ቤታቸው በመመለስ ላይ የነበሩ ናቸው ብለዋል፡፡

አደጋውን ያደረሱት ከወልቂጤ ወደ ሆሳዕና ተከታትለው ሲጓዙ የነበሩ ሁለት መለስተኛ የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች መሆናቸውን እና አሽከርካሪዎቹ ለጊዜው መሠወራቸውን ጠቁመዋል፡፡

የመጀመሪያው ተሸከርካሪ ከባለሦስት እግር ተሽከርካሪ ጋር በመጋጨቱ ከባለሦስት እግር አሽከርካሪው በስተቀር ሁሉም ተሳፋሪዎች ሕይወታቸው ማለፉን አስረድተዋል፡፡

ሕይወታቸው ያለፉትን ጨምሮ እና መጠነኛ ጉዳት የደረሰበትን የባለ ሦስት እግር አሽከርካሪ ለማንሳት በአካባቢው ያሉ ሰዎች ርብርብ በማድረግ ላይ ሳሉም ተከታትለው ሲጓዙ ከነበሩት በሁለተኛው ተሽከርካሪ መገጨታቸውን አዛዡ አረጋግጠዋል፡፡

በዕለቱ በአጠቃላይ የዘጠኝ ሰዎች ሕይወት ማለፉን ተቅሰው ÷ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሕክምና ከገቡ ሰባት ሰዎች መካከል ዛሬ አመሻሽ የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉን ተናግረዋል፡፡

በዚህም የሟቾች ቁጥር ወደ አሥር ማሻቀቡን ጠቁመው ÷ ሁሉም ሴቶች መሆናቸውን እና ሁለቱ ነፍሰጡር ስለመሆናቸው አመላክተዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

Exit mobile version