አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል በነገው ዕለት በአንድ ጀንበር 3 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ግብርናና ተፈጥሮ ኃብት ቢሮ አስታወቀ።
በቢሮው የደን ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ ተስፋይ ተክለኃይማኖት÷ በአንድ ጀንበር 3 ሚሊየን ችግኞች በ1 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ እንደሚተከሉ ተናግረዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን በ45 ወረዳዎች የሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር የፌዴራል ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎችና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች በተገኙበት በፅራእ ወንበርታ ወረዳ በይፋ እንደሚጀመርም ተናግረዋል።
በመርሀ-ግብሩ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ አመላክተዋል።
ሃላፊው በክልሉ በ64 የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች የተዘጋጁ እና ኢኮኖሚያዊ እና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ከ10 ሚሊየን በላይ ችግኞች በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር እንደሚተከሉ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡