Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የተለያዩ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ህብረተሰቡ በአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)  የሀረሪ እና የሲዳማ ክልል ርእሳነ መስተዳድሮች  በነገው እለት ለሚከናወነው በአንድ ጀንበር  ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ ህብረተሰቡ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቀረቡ፡፡

የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ÷በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብሩ ላይ መሳተፍ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር እና ለትውልድ ለማስተላለፍ እጅግ አስፈላጊ ተግባር መሆኑን አንስተዋል፡፡

መርሃግብሩ ላለፉት አመታት እንዳደረግነው ሁሉ ነገም የሀይማኖት፣ የብሔርና የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ሳይገድበን በነቂስ በመውጣት ስለሀገራችን ብለን የምንሳተፍበት ተግባር ነው ብለዋል።

በመሆኑም የሀረሪ ህዝብ ነገ ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ  በተዘጋጁ የችግኝ የመትከያ ስፍራዎች  ችግኝ በመትከል ሀገራዊ ሀላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ ማቅረባቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በተጨማሪ ነገ በሚካሄደው ሀገር አቀፍ የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህዝብ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ ነገ በሚካሄደው የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር መሰረት በማድረግ በክልሉ 10 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል መታቀዱን አመልክተዋል፡፡

እንዲሁም  ህብረተሰቡ በአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ ላይ በንቃት በመሳተፍ አረንጓዴ አሻራውን በማሳረፍ ሀገራዊ ግዴታውን እንዲወጣ የሲዳማ ክልል ግብርና ቢሮ ጥሪ ማቅረቡን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በቢሮው የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ወንድወሰን ቦልካ እንደገለጹት በክልሉ ነገ በአንድ ጀንበር ብቻ 25 ሚሊየን ችግኞች ይተከላሉ።

Exit mobile version