አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች እና ሰራተኞች ዛሬ እየተከናወነ በሚገኘው በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዪንችግኝ የመትከል መርሐ ግብር ላይ ተሳተፉ።
በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በትዊተር ገፁ÷ የአየር ንብረት ለውጥ ድንበር እንደማይገድበው ሁሉ የአረንጓዴ አሻራም ወሰን የለውም ብሏል፡፡
ኢትዮጵያ እና ጂቡቲ በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ በጋራ እየሰሩ መሆኑን የጠቆመው ኤምባሲው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን በጂቡቲ አረጓዴ አሻራቸውን ማሳረፋቸውን አስታወሷል፡፡
በተመሳሳይ በጋና የኢትዮጵያ ኤምባሲ “ነገን ዛሬ እንትከል” በሚል መሪ ቃል በሃገር ደረጃ እየተከናወነ ባለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተሳትፏል፡፡
በህንድ የኢትዮጵያ ኤምባሲም አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶችና የኤምባሲው ሰራተኞችን በማሳተፍ አረንጓዴ አሻራ ማኖር እንደተቻለ በትዊተር ገጹ አመልክቷል።
በተጨማሪም በአንድ ጀምበር 500 ሚሊዮን የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሀ-ግብር በጣሊያን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ኤምባሲ ሰራተኞች ተከናውኗል፡፡
አምባሳደር ደሚቱ ሀምቢሳ በመርሃ ግበሩ እንዳሉት ÷የአረንጓዴ አሻራ ምርሃ ግብር ትልቅ ዓለም አቀፋዊ ዕውቅናን ያተረፈ ተግባር መሆኑን ገልፀዋል፡፡