Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሕብረት ከተነሳን ወርቃማ ውጤት ለማስመዝገብ የሚያግደን ምድራዊ ሃይል የለም – አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በህብረት ስንቆም ከባድ ሚመስለውን ነገር ማሳካት እጅግ ቀላል ነው ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ተናገሩ፡፡

አቶ አደም ፋራህ በዛሬው ዕለት በስኬት የተጠናቀቀውን በአንድ ጀንበር 500 ሚሊየን ችግኝ የመትከል መርሐ ግብር አስመልክተው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም÷ለሀገራችን ኢትዮጵያ ከባድ የሚመስለውን ነገር ግን በሕብረት ስንቆም እጅግ ቀላል የሆነውን ድል በዛሬው ዕለት 500 ሚሊየን ችግኞችን በመትከል አዲስ ሪከርድ አስመዝገበናል ብለዋል፡፡

ይህ ድል እውን እንዲሆን ህጻን አዋቂ ሳንል፣በብሔር እና በጎሳ ሳንከፋፈል፣በፆታ እና በፖለቲካ አስተሳሰብ ሳንገደብ የኢትዮጵያ መጻኢ ተስፋ የለመለመ እንዲሆን በአንድ ቆመናል ሲሉ ተናግረዋል።

የብልፅግና ፓርቲ እንደ ሀገር የቀረበውን ጥሪ በመቀበል  መላው የፓርቲው አመራሮች፣ደጋፊዎች እና አባላት ከጠዋት ጀምሮ ችግኝ ሲተክሉ መዋላቸውን አንስተዋል፡፡

የልፋታችን ፍሬ አፍርቶ እንደ ሀገር የያዝነው 500 ሚሊየን ችግኞችን የመትከል እቅድ፣ ከእቅድ በላይ መሳካቱን ስንሰማ ደስታችን እጥፍ ድርብ ሆኗል ነው ያሉት አቶ አደም።

ያሳካነው ብሔራዊ ድል እኛ ኢትዮጵያውያን “የድር ቢያብር አንበሳ ያስር” ብሂል ባለቤቶች በሕብረት ከተነሳን ወርቃማ ውጤት ለማስመዝገብ የሚያግደን ምድራዊ ሀይል እንደሌለ የሚያሳይ ሁነኛ ምሳሌ ነው ሲሉ አውስተዋል፡፡

ስኬቱ እንዲመዘገብ  ርብርብ ላደረጉ ኢትዮጵያውያን በብልፅግና ፓርቲ አመራር፣ አባላት እና ደጋፊዎች ስም የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

Exit mobile version