አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል እስከአሁን 652 ሺህ ሄክታሩ በሩዝ መሸፈኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡
አቶ ሽመልስ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ በክልሉ ከሁለት ዓመታት በፊት ከ6 ሺህ ሄክታር በታች የተጀመረው የሩዝ ልማት ኢኒሼቲቭ ባለፈው ዓመት 100 ሺህ ሄክታር መድረሱን አስገንዝበዋል፡፡
በዚህ ዓመትም 1 ሚሊየን ሄክታር መሬት በሩዝ ለመሸፈን ታቅዶ እየተሠራ ስለመሆኑ አመላክተዋል፡፡
በመኸር ወቅትም ከ700 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ተዘጋጅቶ ÷ እስከአሁን 652 ሺህ ሄክታር መሬት በሩዝ መሸፈኑን ጠቅሰዋል፡፡
የነገይቷ ኢትዮጵያ ብልጽግና የሚሳካው የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት ላለፉት ጥቂት ዓመታት በለውጡ አመራር የተቀረፁ የተለያዩ ኢኒሼቲቮችን ወደ ሥራ ማስገባቱንም ነው ያስረዱት፡፡
ይህም በብዛት ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን ከመቀነስና ከማስቀረት በተጨማሪ በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ማገዙን አንስተዋል፡፡