Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች እያስመረቀ ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ በ4ኛ ዙር በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ዲግሪ መርሐ ግብር ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች እያስመረቀ ነው፡፡

ዩኒቨርሲቲው በዛሬው እለት በመደበኛ ትምህርት መርሐ ግብር በስድስት ኮሌጆች በምህንድስና እና ቴክኖሎጂ፣ ተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ፣ ግብርና እና ምግብና አየር ንብረት ሳይንስ፣ ማህበራዊና ሰብዓዊ ሳይንስ፣ በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ እንዲሁም በትምህርትና ስነ ባህሪ ሳይንስ በ27 የትምህር ፕሮግራሞች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ነው እያስመረቀ የሚገኘው፡፡

ዩኒቨርሲቲው 640 ተማሪዎች በመደበኛና በመጀመሪያ እንዲሁም በሁለተኛ ዲግሪ፣ 79 በከፍተኛ ዲፕሎማ ፕሮግራም በመምህርነት፣ 31 በከፍተኛ ዲፕሎማ ፕሮግራም የአማራ ፖሊስ ኮሌጅ በመምህርነት በድምሩ 754 ተማሪዎችን ዛሬ ያስመርቃል፡፡

በእለቱ ለአመታት ኢትዮጵያውያን የናፈቋትና የሚወዷት እንዲሁም የኢትዮጵያውያን ፍቅር የተገመደበት መቻቻል፣ መዋደድና አንድነት የተሰበከበትን ሙዚቃ ለሰራችው የጥበብ ፈርጥ ለእጅጋየሁ ሺባባው (ጂጂ) የክብር ዶክትሬት እንደሚሰጣት ተጠቅሷል፡፡

እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ባሉት ኮሌጆች በተለይም በግብርና ምግብና አየር ንብረት ሳይንስ ኮሌጅ፣ ተፈጥሮና ሳይንስ ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ፣ በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ፣ በትምህርትና ስነ ባህሪ ኮሌጅ፣ ማህበራዊና ሰብዓዊ ሳይንስ ኮሌጅ እንዲሁም ሕክምናና ጤና ሳይንስ፣ ምህንድስና እና ቴክኖሎጂ ሳይንስ ኮሌጆች ትምህርት የሚሰጥባቸው ናቸው ተብሏል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በ2015 በተደረጉ የማስፋፊያ ስራዎች 3ኛ ዲግሪን ጨምሮ በቅድመ ምረቃ 59 እና በድህረ ምረቃ 47 ፕሮግራሞችን በማደራጀት ከ18 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛ እና በተከታታይ እያስተማረ የሚገኝ ተቋም ነው ተብሏል፡፡

በየሻምበል ምሕረት

Exit mobile version