Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የተተከሉ ችግኞችን መከታተል ከሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ ነው – መንግስት

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተተከሉ ችግኞችን መከታተል ከሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡

አገልግሎቱ ‘’ማቀድ፤ መተግበር፤ ማሳካት ቀጥሎም መከታተል!’’ በሚል ባወጣው መረጃ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የክረምት ወቅት ሲመጣ በሀገራችን የተለመዱ እና እንደ ባህል እያደጉ የመጡ ሁለት ሃገራዊ ተግባራት እንዳሉ አንስቷል፡፡

እነዚህም፥ የአረንጓዴ አሻራ እና የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ናቸው፡፡

ሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር “ነገን ዛሬ እንትከል” በሚል መሪ ቃል ሰኔ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ተጀምሯል።

ሐምሌ 10 ቀን ደግሞ በአንድ ጀንበር 567 ሚሊየን ያህል ችግኝ በ9 ሺህ 500 የመትከያ ጣቢያዎች መተከሉም የሚታወስ ሲሆን ፥ በዚህ ታላቅ ተግባር ላይ ከ34 ሚሊየን በላይ ዜጎች ተሳትፈውበታል።

በዚህም ያቀድነውንም በስኬት ፈፅመናል! ሲል መንገስት ይገልጻል፡፡

በቀጣይ አንድ ወር ከአስራ አምስት ቀናት ብዙ ሥራዎች ይጠብቁናል ያለው አገልግሎቱ ፥ በተለይም የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ፣ የክረምት የማጠናከሪያ ትምህርት፣ የክረምት የበጎ ፈቃድ የትራፊክ አገልግሎት ሥራዎች እና ሌሎችም የበጎ ፈቃድ ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አንስቷል፡፡

በዚህም መስራትና ለውጥ ማምጣት ይቻላል! ይላል፡፡

አቅደን ሰርተን ማሳካት እንደምንችል በ500 ሚሊየን የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ አሳይተናል ያለው መረጃው ፥ ከሁሉም በላይ ደግሞ እኔ እንደ ዜጋ ለሀገሬ ምን ላበረክት እችላለሁ? ብሎ በቀና ልብ እና በእውነተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት ለተግባር መነሳትን እንደሚጠይቅም ነው ያነሳው፡፡

ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም የተተከሉ ችግኞች በቀጣይ ክትትልና እንክብካቤ እንደሚፈልጉም መንግስት ገልጿል፡፡

መትከል እና እቅድን ማሳካት አንድ ውጤት መሆኑን ገልጾም፥ ይህንን መከታተልና የሚፈለገው ደረጃ ላይ ማድረስ ደግሞ ቀጣዩ ትኩረት የሚሰጠው ተግባር መሆኑም ነው የተመላከተው፡፡

የተተከሉ ችግኞች ከእንስሳት እንዲጠበቁ ማድረግ፣ እንዳይነቀሉ መከታተል በተከላው ከተሳተፉ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሚጠበቅ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

በዚህም የዘርፉ ባለሙያዎች ደግሞ በልዩ ትኩረት ሊሰሩበት እንደሚገባም ነው የተጠቀሰው፡፡

ከ3 ሺህ በላይ የመገናኛ ብዙኃን ሐምሌ 10 ቀን የአንድ ጀንበር 500 ሚሊየን ችግኝ ተከላን ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው በልዩ ሁኔታ እንደዘገቡት ሁሉ የዚህን ሀገራዊ ተግባር ቀጣይነት መከታተል ይጠበቅባቸዋል ብሏል።

የተተከለው ችግኝ ከምን ደረሰ? እያሉ በመከታታል የሚሊዮኖች ተሳትፎ የታየበትን ሀገራዊ ስራ ውጤት በየጊዜው ለህዝብ ሊያሳዩ እንደሚገባም ከአገልግሎቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

Exit mobile version