አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጡት ካንሰር የሚከሰተው ከቁጥጥር ውጭ በሆነ መንገድ በጡት ውስጥ ያሉ ሕዋሳት አድገው እና ተከፋፍለው ዕጢ ሲፈጥሩ ነው።
እንደሌሎች ካንሰሮች የጡት ካንሰር በጡት ዙሪያ ወደሚገኝ ቲሹ ውስጥ ገብቶ ሊያድግ እና ሊሰራጭ ይችላል።
ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎችም በመጓዝ አዳዲስ ዕጢዎችን ሊፈጥር ይችላል።
የጡት ካንሰር በሴቶች ላይ ከሚከሰቱት የካንሰር አይነቶች አንዱ ሲሆን÷ ከቆዳ ካንሰር ቀጥሎ በብዛት ከሚከሰቱ ካንሰሮች ውስጥ በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ለመሆኑ የጡት ካንሰር አጋላጭ የሆኑ ምክንያቶች ምንድናቸው?
ብዙውን ጊዜ ከ 50 ዓመት በላይ በሆኑ ሴቶች ላይ የሚከሰት ሲሆን÷ ሲጋራ እና አልኮል መጠቀም ፣ ከልክ ያለፈ ውፍረት ፣ የሆርሞን ወሊድ መከላከያ ወይም ሌላ የሆርሞን መድሃኒት ለረጅም ጊዜ መጠቀም እና የጨረር ህክምና ለጡት ካንሰር ተጋላጭ ያደርጋሉ።
በተጨማሪም በቤተሰብ ውስጥ የጡት ካንሰር መኖር፣ አለመውለድ ወይም የመጀመሪያ ልጅን ከ30 አመት በኋላ መውለድ፣ ከወለዱ በኋላ ጡት አለማጥባት፣ ከ12 ዓመት እድሜ በፊት የወር አበባ መምጣት እና ከ 55 ዓመት እድሜ በኋላ የወር አበባ ዘግይቶ መቆም እንደ መንስኤ ሊወሰዱ ይችላሉ።