Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሰባት ጊዜ የምርቃት ካባ የለበሱ ብርቱ ሰው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ትምህርት ማለቂያ የለውም ይባላል። ብዙዎች የትምህርት ቤት ቆይታቸውን ጨርሰው ከተመረቁ በኋላ ተመልሰው የትምህርት ቤት ደጃፍን መርገጥ ዳገት ይሆንባቸዋል። ጥቂቶች ደግሞ ከትምህርት ተቋማት ሳይርቂ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ዕውቀትን በመሸመት ለዓለም ያላቸውን ግንዛቤ በማሳደግ የህይወት ዘይቤያቸውን ቀለል ለማድረግ ይተጋሉ።

ላለፉት 17 አመታት በንግድ ባንክ እያገለገሉ የሚገኙት አቶ ነብዩ ሰለሞን ከትምህርት ቤት ከማይርቁት ጥቂቶች መካከል ናቸው።

አቶ ነብዩ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመመረቅ ለሰባተኛ ጊዜ የመመረቂያ ካባ ደርበዋል።

5 የመጀመሪያ ዲግሪ እና ሁለት የሁለተኛ ዲግሪ የያዙት አቶ ነብዩ፤ በህግ፣ በአካውንቲንግ፣ ኢኮኖሚክስት፣ ማናጅመነት እና ሳኮሎጂ በዲግሪ ተመረቁ ሲሆን ዛሬ ደግሞ ለሁለተኛ ሁለተኛ ዲግሪ ምርቃታቸው ደምቀው ተገኝተዋል፡፡ስራ ከጀመርኩበት ጊዜ አንስቶ ከትምህርት ቤት የራቅኩበት ጊዜ መኖሩን አላስታውስም የሚሉት አቶ ነብዩ፤ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች እውቀት እና ክህሎት ማዳበራቸው ለስራቸው መቃናት እንደጠቀማቸው ይገልጻሉ።

ስልጠናዎች ሲሰጡም በተለያየ ዘርፍ ያገኙትን እውቀት እንደማጣፈጫ ይጠቀሙበታል፡፡

እነዚህን ትምህርቶች ስማር እራሴን ካልባሌ ነገሮች እንዳርቅ እና ጊዜዬንም በአግባቡ እንድጠቀም አግዞኛል የሚሉት አቶ ነብዩ፤ በቀጣይ የሶስተኛ ዲግሪ ለመያዝ ትምህርት የመቀጠል ፍላጎት እንዳላቸውና ለዚህም እየተዘጋጁ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ባለትዳርና የሶስት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ነብዩ በትምህርት መስክ ላስመዘገቡት ስኬት የቤተሰቦቻቸው ድርሻ የጎላ በመሆኑ ምስጋናቸው ከፍ ያለ ነው።

የትዳር አጋራቸው ወ/ሮ ህይወት ነጋሽ ጓደኞቻቸው ሀይለአብ ካሳዬ እና ዮሴፍ ተክሌ እንደሚመሰክሩት የአቶ ነብዩ የመማር ፍቅር የተለየ ነው።

የጊዜ አጠቃቀም ልምዳቸውም ለሌሎች ትምህርት የሚሆን እንደሆነ ጠቅሰው፤ ትምህረት ለስራ ማግኛ ብቻ ሳይሆን አኗኗርን ለማዘመን፣ በስራ ላይ እሴት ለመጨመርና የበለጠ ውጤታማ ለመሆን ይረዳል ይላሉ፡፡

በማርታ ጌታቸው

 

Exit mobile version