Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ናፍቆት የድሬዳዋ ሣምንት መከበር ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በየዓመቱ ሐምሌ ወር ላይ የሚከበረው ናፍቆት የድሬዳዋ ሣምንት መከበር መጀመሩን የአስተዳደሩ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ፡፡

ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘው ናፍቆት የድሬዳዋ ሣምንት እስከ ሐምሌ 20 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚዘልቅ ተገልጿል፡፡

በአከባበሩም በሀገር ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች እና በውጭ ሀገር የሚኖሩ የድሬዳዋ ተወላጆች እንዲሁም በተለያዩ ዘርፎች ለድሬዳዋ ዕድገት አስተዋጽኦ ያበረከቱ ወዳጆች ተገኝተዋል ብሏል ቢሮው፡፡

በተለያዩ ምክንያቶች ተራርቀው የሚኖሩ ቤተሰቦች በዓመት አንድ ጊዜ የሚገናኙበት አከባበሩ ልዩ ልዩ ግቦች እንዳሉት ነው የተመለከተው፡፡

በመንግሥት፣ በከተማዋ ነዋሪዎች እና በአጋር ድርጅቶች እየተከናወኑ የሚገኙ ዘርፈ- ብዙ የልማት ሥራዎችን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ያሉ ተወላጆችና ወዳጆች እንዲያግዙ ማድረግ የአከባበሩ ዓላማ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

ለበዓሉ ተሳታፊዎች ትናንት ምሽት በአሥተዳደሩ የእራት ግብዣ መደረጉ እና ዛሬ በተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮች አከባበሩ እንደሚቀጥል ነው የተመላከተው፡፡

በነገው ዕለትም የተለያዩ ፕሮጀክቶች እንደሚመረቁ ተጠቁሟል፡፡

“ናፍቆት የድሬዳዋ ሣምንት” ከድሬዳዋ ርቀውና ኑሯቸውን ሌላ ቦታ ያደረጉ ወገኖች በዓመት አንድ ጊዜ በናፍቆት የሚገናኙበትን ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ የተሰጠ ስያሜ መሆኑንም ነው ቢሮው ያስታወቀው፡፡

በዮሐንስ ደርበው

Exit mobile version