Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በጋምቤላ የ12ኛ ክፍል ፈተናን ለማስፈጸም በቂ ዝግጅት ተደርጓል – የክልሉ መንግሥት

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል የ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ያለምንም የፀጥታ ችግር ለማስፈጸም የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ፡፡

በፈተናው ወቅት አስፈላጊውን ጥበቃና ክትትል የሚያደርግ በቂ የፌዴራል የጸጥታ ኃይል መመደቡ ተገልጿል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና የፈተናው ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ኡሞድ ኡጁሉ÷ በክልሉ ሰሞኑን ተከስቶ የነበረው የፀጥታ መደፍረስ የክልሉ መንግስት ከፌዴራል የፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት ባከናወነው ስራ ሰላም እየሰፈነ መጥቷል ብለዋል።

በዚህም የክልሉ መንግስት ፈተናውን ስኬታማ በሆነ መልኩ ለመስጠት ከፌዴራል የፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡

ተማሪዎች በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ በወቅቱ እንዲደርሱ ከክልሉ ትራንስፖርት ቢሮ ጋር በመቀናጀት የትራንስፖርት አቅርቦት ከዛሬ ጀምሮ መመቻቸቱንም ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የተናገሩት፡፡

በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ መልዕክቶች ግጭት ቀስቃሽና የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘቡ ናቸው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ በአሁኑ ሰዓት ፈተናውን በተረጋጋ ሁኔታ ለመውሰድ የሚያስችል የተሻለ መረጋጋት እንዳለ አረጋግጠዋል፡፡

ወላጆችም ያለምንም ስጋት ልጆቻቸውን ወደ ፈተና ማዕከሉ እንዲልኩ ጥሪ አቅርበዋል።

የዲማ፣ ጎደሬ እና መንገሺ ወረዳዎች ተፈታኞች በአቅራቢያቸው በሚገኘው የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ቀሪ የክልሉ ወረዳዎች በጋምቤላ ዩኒቨርስቲ ፈተናቸውን ይወስዳሉ ተብሏል፡፡

 

በሌላ በኩል በጋምቤላ ክልል ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሚናቸውን መወጣት እንደሚኖርባቸው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አሳስበዋል።

አቶ ኡሞድ በጋምቤላ ክልል ተከስቶ በነበረው የፀጥታ መደፍረስ ዙርያ ከአምስቱም ቀበሌዎች ከተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱም በክልሉ ዘላቂ ሰላም ማምጣት በሚቻልበት ሁኔታና የህዝቡን የእርስ በርስ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሀኔታም ትኩረት አድርገው መክረዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በክልሉ አስተማማኝ ሰላም እንዲኖር ሚናቸው የጎላ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።

 

Exit mobile version