አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የ”ኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን” በደቡብ ኦሞ ሐመር እና በና-ፀማይ ወረዳዎች የጤና ልማት ሥራዎችን ለማገዝ ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ሁለት አምቡላንስና አራት የአልትራሳውንድ ማሽኖችን ድጋፍ አደረገ።
የፋውንዴሽኑ መስራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ ጂንካ ከተማ ተገኝተው ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንደገለጹት፣ ድጋፉ በሐመር እና በና-ፀማይ ወረዳዎች ለሚገኙ ስድስት ጤና ጣቢያዎች ለጤና አገልግሎት እንዲውል ታስቦ የተደረገ ነው።
በድጋፉ እያንዳንዳቸው ግምታዊ ዋጋቸው 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሆኑ ሁለት አምቡላንሶች እንዲሁም የአንዱ ዋጋ 1 ሚሊየን ብር የሆነ አራት የአልትራሳውንድ መሳሪያዎች ከነ መለዋወጫቸው መካተታቸው ገልጸዋል።
በአጠቃላይ ለድጋፉ ከ13 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉን የተናገሩት ወይዘሮ ሮማን፣ “የተሽከርካሪና የመሳሪያ ድጋፉ በወረዳዎቹ የጤና ልማት ስራዎችን ከማገዝ አኳያ ትልቅ ሚና አላቸው” ብለዋል።
የደቡብ ኦሞ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ካይ በበኩላቸው÷ድጋፉ የጤና ጣቢያዎችን አቅም እንደሚያሳድገው መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የሐመር ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ፎራ ጋርሾ ድጋፉን በተረከቡበት ወቅት የዛሬው የአምቡላንስና የህክምና መሳሪያ ድጋፍ ቀልጣፋ የጤና አገልግሎት ለመስጠት ስለሚያስችል የነበረውን የአንቡላንስ ችግር በተወሰነ መልኩ ይፈታዋል ብለዋል።
የበና-ፀማይ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ኢያኮ ጃርታ በበኩላቸው÷ በወረዳው ያሉ አምቡላንሶች ውስን በመሆናቸው ምክንያት በወሊድና በድንገተኛ አደጋ ወቅት ፈጥኖ ለመድረስ እንደሚቸገሩ ገልፀው ዛሬ የተደረገው ድጋፍ ችግሩን በተወሰነ መልኩ እንደሚያቃልል ተናግረዋል።