Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በ12ኛ ክፍል ፈተና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን የሀረሪ ክልል ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በክልሉ በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ፈተና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን የሀረሪ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ ሙክታር ሳሊህ እንደገለፁት÷ ባለፈው አመት እንደሀገርም እንደ ክልልም የተመዘገበው የ12ኛ ክፍል ውጤት ዝቅተኛ ነበር፡፡

ባለፈው አመት በክልሉ ፈተናውን ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል 10 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆኑት ተማሪዎች ብቻ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሚያስገባቸውን ውጤት ማስመዝገባቸውን አስታውሰዋል።

ዘንድሮ ከባለፈው አመት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን ያነሱት ሃላፊው በዋናነትም ተማሪዎችን የማብቃትና የመደገፍ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

በተለይም ከመደበኛ የትምህርት ጊዜ ባሻገር በተቃራኒ ፈረቃ እና በእረፍት ቀናት የማጠናከሪያ ትምህርት፣ ሞዴል ፈተናዎችን እንዲሁም የቤተመፅሐፍት አገልግሎት ጊዜን የማሳደግና ሌሎች ድጋፎች ሲደረጉ መቆየታቸውን አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር ከወላጆች ጋር ውይይት የማድረግና ተማሪዎችን በስነምግባር የማዘጋጀት ስራ ሌላው ትኩረት ተሰጥቶት ሲሰራ የቆየ ተግባር መሆኑን ነው ያብራሩት ።

በዘንድሮው ዓመት በክልሉ በሚገኙ 14 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 2 ሺህ 510 ተማሪዎች የዘንድሮውን የ12 ክፍል ብሔራዊ ፈተና እንደሚወስዱ መግለፃቸውን ከሀረሪ ክልል ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version