አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና እና ኬንያ የ”ቤልት ኤንድ ሮድ” ትብብራቸውን ለማጠናከር መስማማታቸው ተገለጸ፡፡
የቻይናው የውጭ ጉዳይ ኮሚሽን ዳይሬክተር ዋንግ ዪ ከኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ጋር በናይሮቢ ተገናኝተው ሀገራቱ የቤልት ኤንድ ሮድ ትብብራቸውን ማጠናከር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል፡፡
ዋንግ ዪ ÷ ቻይና ከኬንያ ጋር ለ60 ዓመታት የዘለቀ ስትራቴጂያዊ ግንኙነት እንዳላት ጠቅሰው፥ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበትን ይህን የምሥረታ ቀን እያከበሩ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይም በልማት እና በሌሎች በርካታ ዘርፎች አጋርነታቸውን ይበልጥ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚሠሩ ጨምረው ገልጸዋል።
ኬንያ የምትከተለውን ከሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎቿ ጋር የተጣጣመ የዕድገት ጎዳና ቻይና በፅኑ እንደምትደግፍም ነው ዋንግ ዪ የተናገሩት፡፡
በ”ቤልት ኤንድ ሮድ መርሐ-ግብር” ÷ ቻይና ከኬንያ ጋር በባቡር፣ በመንገድ መሠረተ-ልማት ፣ በአየር ትራንስፖርት ፣ በመረጃና በሌሎችም ዘርፎች በትብብር መሥራቷን እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
የቻይና-አፍሪካ የትብብር ፎረም መርሐ-ግብሮች በማሳደግ አኅጉራዊ ውኅደትን ዕውን ለማድረግ እንደሚሠሩም ተናግረዋል።
የ”ቤልት ኤንድ ሮድ” መርሐ-ግብር የተጀመረው ቻይናን ጨምሮ 149 ሀገራት በፈረንጆቹ መጋቢት ወር 2022 ላይ በተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት ሠነድ ነው፡፡
ሐሳቡ በቻይና አነሳሽነት የቀረበ ሲሆን ዓላማውም እስያ ፣ አፍሪካንና አውሮፓን በምድር እና በባሕር በሚዘረጋ የመሠረተ-ልማት ግንባታ ማስተሳሰር ነው፡፡
በመርሐ-ግብሩ ቀጣናዊ እና አኅጉራዊ ግንኙነትን በማጠናከር የንግድ ግንኙነትን ለማስፋት እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማነቃቃት እየተሠራም ነው፡፡
በዚሁ በቻይና የ”ቤልት ኤንድ ሮድ” መርሐ-ግብር ኢትዮጵያም ንቁ ተሳታፊ ሆና እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች፡፡