Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የስቴም ትምህርትን በአፍሪካ ለማበረታታት አዲስ ትምህርት ቤት ተከፈተ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የስቴም ትምህርትን በአፍሪካ ለማበረታታት የሚያስችል አዲስ ትምህርት ቤት መከፈቱ ተገለጸ፡፡
 
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦይንግ እና ቲንክ ያንግ ጋር በመተባበር በአፍሪካ ታዳጊ ወጣቶች በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና እና ሂሳብ (ስቴም) የከፍተኛ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ለማድረግ ያለመ አዲስ ትምህርት ቤት መክፈቱን አስታውቋል።
 
በኢትዮጵያ አየር መንገድ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ የሚሰጠው ስቴም ትምህርት ለስድስት ሳምንታት የሚቆይ ሲሆን÷ ከ300 ሰአታት በላይ ትምህርትና ስልጠና ይሰጣል።
 
መርሃ ግብሩ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች የተውጣጡ 24 ተማሪዎችን ለመቀበል የተዘጋጀ ሲሆን÷ ከዚህም ውስጥ 50 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች እንደሚሆኑ ተጠቁሟል፡፡
 
በተጨማሪም መምህራን የላቀ የስቴም ፅንሰ ሀሳቦችን ለማስረፅ የሚያግዙ አስፈላጊ መሳሪያዎችን እንዲታጠቁ ለማስቻል የመምህራን ስልጠና መርሃ ግብር ለመስጠት መዘጋጀቱንም አስታውቋል።
 
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው÷ “የኢትዮጵያ ወጣቶች በትምህርት እና በቀጣይ ስራቸው በዋናነት በአቪዬሽን ዘርፍ ስኬታማ እና የስራ ፈጣሪዎች እንዲሆኑ የሚረዳውን የስቴም ትምህርት ቤት ከቦይንግ እና ቲንክ ያንግ ጋር በመተባበር በማስጀመራችን ደስተኛ ነን” ሲሉ መግለፃቸውን ስኪፍት ዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡
 
ከቴክኖሎጂ ጋር በተመጣጣኝ ፍጥነት መሄድ እና ለወደፊት ፍላጎቶች በመዘጋጀት እናምናለን ያሉት አቶ መስፍን÷ ይህ ትብብር እና ተነሳሽነት ወጣቶችን በማጎልበት በፍጥነት እያደገ ያለውን የኢትዮጵያ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ የወደፊት ፍላጎቶችን ለማሟላት ያስችላል ብለዋል፡፡
Exit mobile version