Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ ከሴራሊዮን ጋር ያላት ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር ትፈልጋለች- አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከሴራሊዮን ጋር ያላትን የሁለትዮሽ፣ አህጉራዊ እና የባለብዙ ወገን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር እንደምትፈልግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን ከሴራሊዮን ፕሬዚዳንት ጁሊየስ ማዳ ቢዮ (ዶ/ር) ጋር÷ የሁለቱ ሀገራት የጋራ ፍላጎቶች በሆኑ በሁለትዮሽ፣ አህጉራዊ እና የባለብዙ ወገን ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

የሀገራቱ መንግስታት በተለያዩ መስኮች እያከናወኗቸው ባሏቸው ስራዎች ያስመዘገቧቸውን ስኬቶች አስመልክቶ መወያየታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

አቶ ደመቀ የኢትዮጵያ መንግስት እያከናወናቸው ያሉትን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር፣ የሌማት ትሩፋት፣ የስንዴ ምርት እና “ትምህርት ለትውልድ” ንቅናቄ አስመልክቶ ለፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ጁሊየስ ማዳ ቢዮ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ከሰው ኃይል ልማት ጋር የተቆራኘውን የምግብ ዋስትና፣ ግብርና እና ጤና ስራዎች አስመልክቶ የሀገራቸውን ተሞክሮ አጋርተዋል።

በተመሳሳይ አቶ ደመቀ መኮንን ከማላዊው ፕሬዚዳንት ላዛሩስ ቻክዌራ (ዶ/ር) ጋር የሁለትዮሽ ትብብርን ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም በሁለትዮሽ፣ አህጉራዊ እና የባለብዙ ወገን ትብብሮችን ይልጥ ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version