አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በ2016 በጀት ዓመት 7 ነጥብ 5 ሚሊየን ተማሪዎችን የትምህርት ቤት ምገባ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡
በቢሮው የእቅድና በጀት ዝግጅት ዳይሬክተር ሃሰን እንድሪስ እንዳሉት፥ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ተማሪዎች በተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ምክንያቶች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ አስፈላጊው ክትትል ተደርጓል፡፡
ለዚህም በክልሉ በአዲስ መልክ የተጀመረው የትምህር ቤት ምገባ አገልግሎት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ነው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የገለጹት፡፡
በ2015 በጀት ዓመት በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ከ5 ጥብ 2 ሚሊየን በላይ ተማሪዎችን የትምህርት ቤት ምገባ አገልግልት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስታውሰዋል፡፡
በመንግስት ት/ቤቶች የሚገኙ ሁሉም የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች እና ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎችም የአገልግሎትተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በ2016 በጀት ዓመትም የምገባ አገልግሎቱን በስፋት ለማዳረስ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን አቶ ሃሰን ገልጸዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ