Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአፍሪካ እና በሩሲያ መካከል ሁሉን አቀፍ ትብብር ለማጠናከር ተስማምተናል – ፕሬዚዳንት ፑቲን

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ ሀገራት እና ሩሲያ መካከል ሁሉን አቀፍ ትብብር ለማጠናከር ስምምነት ላይ ደርሰናል ሲሉ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን ገለፁ።

ፕሬዚዳንቱ ሩሲያ እና አፍሪካ ትብብራቸውን በኢኮኖሚ፣ በንግድ፣ በቴክኖሎጂ፣ በመሰረተ ልማት ግንባታ፣ በትምህርት እና በጤና ዘርፎች ማጠናከር በሚችሉባቸው መንገዶች ላይ ፍሬያማ ውይይቶች ተካሂደዋል ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ፑቲን የሩሲያ አፍሪካ ጉባኤ መጠናቀቅን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፥ በሩሲያ መንግስትና በአፍሪካ ሀገራት መካከል በርካታ ስምምነቶች ተፈጽመዋል።

አፍሪካ በሽታ የመከላከል አቅሟን እንድታጠናክር የሚያግዙ በ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ሩብል የሚተገበሩ ስምንት ፕሮጀክቶች በመንግስታቸው ይፋ መደረጋቸውን እና እስከ ፈረንጆቹ 2026 የሚተገበር የጋራ እቅድ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም አክራሪነት እና አሸባሪነትን በጋራ ለመዋጋት፣ ሰላምንና ጸጥታን ለማረጋገጥ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎችን ለመቀነስ በጋራ መስራት በሚቻሉባቸው መንገዶች ላይ ስምምነት ላይ መደረሱንም ነው የገለጹት።

የሩሲያ ባለሃብቶች በአፍሪካ በስፋት መሰማራት እንዲችሉ እና የአፍሪካ ሃገራትም ምርቶቻቸውን ከቀረጥ ነጻ በሆነ መንገድ ለሩሲያ የሚያቀርቡበት እድል እንደሚፈጠርም አስረድተዋል።

የሩሲያ አፍሪካ ጉባኤ በየሶስት ዓመቱ  እንደሚካሄድም ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።

በወንደሰን አረጋኸኝ

 

Exit mobile version