አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ ከዓለም ንግድ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ንጎዚ ኦኮንጆ (ዶ/ር) ጋር በስዊዘርላንድ ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም÷ አቶ ገብረመስቀል በኢትዮጵያ በንግዱ ዘርፍ እየተከናወኑ ስላሉ የማሻሻያ ስራዎች ገለጻ አድርገዋል፡፡
የዓለም ንግድ ድርጅት የአባልነት ድርድርን ለማጠናቀቅ የኢትዮጵያ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
ንጎዚ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷የዓለም ንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል በሚደረጉ ድርድሮች ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች ሊያገጥሙ እንደሚችሉ አንስተዋል፡፡
እነዚህ ፈተናዎችም በሀገር ውስጥ በሚደረጉ ተከታታይ ውይይቶች እና ከአባል ሀገራት ጋር በሚደረጉ ድርድሮች እንደሚፈቱ ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኢኮኖሚ ያላትን ሚና የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ÷ በሒደት ከዓለም ንግድ ስርዓት ተጠቃሚ መሆን እንደምትችል አብራርተዋል፡፡
በሚኒስትሩ በተደረገው ጉብኝትና ኢትዮጵያ የአባልነት ድርድሩን በድጋሚ ለማስቀጠል ፍላጎት ማሳየቷ እንዳስደሰታቸውም ገልጸዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ የኢትዮጵያን የድርድር ሒደት ለማገዝ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርጉ ቃል መግባታቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡